Friday, February 20, 2015

ጾም

ጾም ማለት ሰውነት ከሚያስፈልጋቸው ነገሮች መከልከል ፣ መወሰን ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት ለሰውነት የሚያምረውን
፣ የሚያስጎመዠውን ነገር ሁሉ መተው ማለት ነው፡፡ የጾም ሃይማኖታዊ ትርጉሙ ፈጣሪን መለመኛ ከኃጢአት ቁራኝነት መለቀቂያ መሣሪያ ስለሆነ በጾም ወራት ለአምሮት ለቅንጦት የሚበሉ ፤ ለመንፈሳዊ ኃይል ተቃራኒ የሆኑ ሥጋዊ ፍትወትን ከሚያበረታቱ የአልኮል መጠጦችን የጥሉላት መባልዕት መታቀብ ይገባል፡፡ ነገር ግን ይህ ብቻ ፆምን ፍጹም አያደርገውም፡፡ አንድ ክርስቲያን በማንኛውም ጊዜ ሕዋሳቱን ሰውንና እግዚአብሔርን ከሚያሳዝኑ ክፉ ሓሳቦችና ተግባራት መቆጠብና መከልከል አለበት ፡፡ የጹም አይን ፣ ይጹም ልሳን ፣ እዝንኒ ይጹም እምሰሚዓ ሕሱም በተፋቅሮ ( ቅ/ያሬድ) ፡፡ በአንጻሩ ደግሞ በመልካም ሥነ ምግባራትና ትሩፋት መታነጽ ይገባዋል፡፡ ጾምን ጾመው የተጠቀሙባት ቅዱሳን አበው ጾም የፀሎት እናት ፣ የእንባ ምንጭ ፣ የፅድቅ መሠረት ብለዋታል፡፡ የጾም ጥቅም ፡-ጸም የሥጋን ምኞት የምታጠፋ ፣ ቁስለ ነፍስን የምታደርቅ ፣ ለጎላማሶች ፀጥታንና መረጋጋትን የምታስተምር ፣ ከእንስሳዊ ግብርና ጠባይ የምትከለክል ፣ ሰው መላእክትን መስሎ የሚኖርባት ደገኛ ሥርዓት ናት፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን (በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን) ሁሉም ክርስቲያን ሊጾማቸው የሚገባ ሰባት የአዋጅ አጽዋማት አሉ፡፡ እነዚህም ፡- ፩.ዓቢይ ጦም ፪. ጾመ ሐዋርያት ፫. ጾመ ፍልሰታ ፬. ጾመ ነቢያት ፭. ጾመ ገሃድ ፮. ጾመ ነነዌ ፯. አርብና ረቡዕ ናቸው፡፡ ዓቢይ ጾም ፡- ከነዚህ ከሰባት አጽዋማት ትልቁና ሰፊ ጊዜ የሚጾመው ዓቢይ ጾም ነው፡፡ ዓቢይ መባሉም ጌታችን መዲኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንቶስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሞ ተላላቅ የሴይጣን ፈተናዎች ድል የተነሱበትና ወደፊትም ድል የሚነሱበት ስለሆነ ነው፡፡ በገደመ ቆሮንቶስ ድል የተነሱ ተላላቅ የሴይጣን ፈተናዎች ሶስቱ አርእስተ ኃጣውእ ይባላሉ፡፡ አነዚህም ፍቅለ ንዋይ ፣ ስስትና ትዕቢት ናቸው፡፡ ዓቢይ ጾም ስምንት ሰምንታት ያሉት ሲሆን እነዚህ ሳምንታት የየራሳቸው ስያሜና ታሪክ አለቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን የዜማ ፈርጥ ኢትዮጰያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ደጓው በዓቢይ ጾም ለሚገኙት እሁዶች የተለየ መዝሙር ስለሠራላቸው እያንዳንዱ እሁድ በመዝሙሩ ይጠራል፡፡ የመጀመርያው እሁድ፡- ዘወረደ አምስተኛው እሁድ፡- ደብረ ዘይት ሁለተኛው እሁድ ፡- ቅድስት ስድስተኛው እሁድ፡- ገብር ሔር ሶስተኛው እሁድ፡- ምኩራብ ሰባተኛው እሁድ፡- ኒቆዲሞስ አራተኛው እሁድ፡- መጻጉዕ ስምንተኛው እሁድ፡- ሆሣዕና ይባላሉ፡፡

No comments:

Post a Comment