Saturday, March 14, 2015

፭. ደብረ ዘይት፡-



አምስተኛው እሑድ ደብረ ዘይት ይባላል፡፡ ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ተራራ ማለት ነው፡፡ ደብረ ዘይት ብዙ የወይራ ዛፍ ያለበት ተራራ ሲሆን ስያሜውንም ያገኘው ከዚሁ ነው፡፡ ጌታ በደብረ ዘይት ተራራ ተቀምጦ ስለዳግም ምጽዓት ወይም የዓለም መጨረሻ ለቅዱሳን ሓዋርያቱ አስተምሯል፡፡ ጌታችን ቅዱሳን ሐዋርያቱን አስከትሎ ከመቅደስ ወጥቶ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሲሄደ ሐዋርያት የሰሎሞንን ቤተ መቅደስ ውበት የድንጋዩን አጠራረብ፣ ንድፈ ሕንፃውን፣ የወርቅ ዝምዝሙን፣ የሓር ጭምጭማቱን አይተው ተደነቁ፡፡ ግታም መልሶ፡- ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው። ይህን ውብ ሕንፃ የነደፉ እጆች በሞት ይታሰራሉ፣ ይሁን ድንቅ ንድፍ ያፈለቀ አእምሮ ይያዛል፤ በድንጋይ የተመሰለ ሕንፃ ሰውነታችሁ ይፈርሳ፣ በሞት ይለወጣል፡፡ ይህች በጨረቃ ደምቃ፣ በከዋክብት አሸብርቃ፣ በፀሓይ ሙቃ በውበቷ ምታማልላቸው ዓለም ታልፋለች አላቸው፡፡

ጌታ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፡- ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ የዓለም መጨረሻው ምልክቱ ይህ ነው፡- ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ ብለው በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ፣ ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፣ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳልና፣ ረብም፣ ቸነፈር፣ የምድርም መናወጥ በልዩልዩ ስፍራ ይሆናል፤ በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፣ ይገድሉአችሁማል፣ ስለስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ ብዙዎች ይሰናከላሉ፣ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጠሉ፣ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፣ ብዙ ሓሰተኞች ነቢያትም ይነሳሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ፣ ከዓመጻም ብዛት የተነሳ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች፡፡ እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን እርሱ ይድናል፡፡ ማቴ. ፳፬ ፥ ፩ - ፲፬፡፡
ምልክቱን ነገረን መምጫውስ መቼ ነው? ስለኝ እንደሆነ፡- ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዳስተማሩን የጌታችን መምጫ ወሩ ወርኃ መገቢት፣ እለቱ እለተ ሰንበት፣ ሰዓቱ እኩለ ሌሊት ነው፡፡ ይህ ዓለም የሚያልፈው በተፈጠረበት በውርኃ መጋቢት ነው፡፡ መጋቢት ፳፱ እለተ ሰንበት እንደተፈጠረ በዚሁ እለት፣ በዚሁ ሰዓት በወርኃ መጋቢት ያልፋል፣ ይጠቀለላል፣ ይፈጸማል፡፡ በወርኃ ጳጉሜም መምጫው ነው የሚሉ ሊቃውንት አሉ፡፡ ነገር ግን በወንጌል እንደ ተናገረው የትኛው ወርኃ መጋቢት፣ የትኛይቱ እለተ ሰንበት፣ ትኛይቱስ እኩለ ሌሊት፣ የትኛዋ ጳጉሜ እንደሆነ ከእርሱ ከእግዚአብሔር በቀር የሚያውቅ ማንም ፍጡር የለም፡፡ ማቴ. ፳፬፥ ፴፰ ልብ ይለዋል፡፡
በዓለ ደብረ ዘይት ከጌታችን አባይት በዓለት አንዱ ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያንም ታላቅ በዓሏ ነው፡፡ ለዓለምም መገኛ፣ መፈጸሚያዋ፣ የእድሜ መለኪያዋ ትልቅ አዝመራዋ በዓሏ ነው፡፡ ወርኃ መጋቢት ከአውርኃ ዓመት ሁሉ የተለየ ነው፡፡
መጋቢት ፳፱ እለተ ሰንበት፡-
ሀ. ዓለም የተፈጠረበት (ፍጥረተ ዓለም)
ለ. የጌታችን ትንሳኤ (ጥንተ ትንሳኤ)
ሐ. ዳግም ምጽዓት (ህልፈተ ዓለም) ነው፡፡      
ደበረ ዘይት ሁሉም የዘራውን የሚያጭድበት፤ የበተነውን የሚሰበስብበት የመኸር ጊዜ ነው፡፡ ደብረ ዘይት ምርቱ ከገለባ፤ ስንዴው ከእንክርዳድ (ፃድቁ ከኃጥኡ) የሚለይበት አውድማ ነው፡፡ ደብረ ዘይት ሁሉም የሥራውን ዋጋ የሚቀበልበት የፍርድ አደባባይ ነው፡፡ ደብረ ዘይት የምግባር መለኪያ፣ የዋጋ መቀበያ፣ የፍት ርትዕ መስጫ አውድ ናት፡፡ ደብረ ዘይት ለፃድቀን የሚፈረድላቸው በኃጥአን የሚፈረባቸው፤ ይግባኝ የማይጠየቅበት በዘለዓማዊ ንጉሥ በአምላካችን ዘለዓለማዊ ፍትህ የሚሰጥበት የፍርድ ቀን ናት፡፡ ደብረ ዘይት ፃድቀን በአምላካቸው በአደባባይ በክብር ደምቀው የሚመሰገኑበት ኃጥአን በሀፍረት ተሸማቀው የሚቀጡባት እለተ ሐሴት ወእለተ ደይን ናት፡፡
ደብረ ዘይት ፃድቃን በፀናች ሃይማኖት በበጎ ምግባር ኣሸብርቀው በአምላካቸው ቀኝ ቆመው ኑ የአበቴ ብሩካን ወደ ተዘጋጀላቸው ዘለዓለማዊ እረፍት ግቡ ሲባሉ ኃጥኣን በክህደት ልቡናቸው በከፋ ሥራቸው አፍረው ከአምላከቸው ግራ በመሆን እናንተ ርጉማን አላውቃችሁም ለሴይጣንና ለሠራዊቱ ወደ ተዘጋጀ የዘለዓለም ፍደ ግቡ የሚባሉባት የሀዘንና የደስታ ቀን ናት ፡፡
የሁላችን እለተ ምፅአታችን እለተ ሞታችን መሆኑን አውቀን በሃይማኖት ፀንተን በጎ ሥራ በመሥራት በቀኝ ለመቆም እንትጋ የማኅቶት የሳምንቱ መልእክት ነው ፡፡
የእለቱ መዝሙር ፡- እንዘ ይነብር እግዚእነ
ምንባብ ፡-፩ተሰ. ፩ ፥ ፲፫ - ፲፰ ፤ ፪ጴጥ. ፫ ፥ ፯ - ፲፭ ፤ የሐዋ. ፳፫ ፥ ፩ – ፰
ምስባክ ፡- እግዚአብሔርሰ ገሀደ ይመጽዕ ወአመላኪነሂ ኢያረምም እሳት ይነድድ ቅድሜሁ ፡፡ መዝ. ፵፱፥፪-፫


ወንጌል ፡- ማቴ. ፳፬ ፥ ፩ - ፲፭



ወስብሐት ለእግዚእብሔር 

No comments:

Post a Comment